በብዛት ሆስፒታል ተመላላሽ ክፍል ወይም ድንገተኛ ክፍል በተለያየ አጋጣሚ ከመውደቅ ወይም ከመኪና አደጋ ጋር በተያያዘ ብዙ ታካሚዎች ይመጣሉ። በዚሁ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ እጃቸው ወይም እግራቸው ላይ ጉዳት ይደርሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የአጥንት ስብራት ወይም ስንጥቃት እንዲሁም የመገጣጠሚያ ውልቃት ያጋጥማቸዋል።

በዚህ ጊዜ መደረግ ያለበት በጊዜ ወደጤና ተቋም ተኬዶ በተገቢው የጤና ባለሞያ መመርመር እና መታከም እንጂ ወደ ባህላዊ ህክምና ወይም በተለምዶ “ወጌሻ” ጋር ሄዶ መታከም መዘዙ ብዙ ነው።

ለምንድነው ወጌሻ ጋር መሄድ የሌለብን የሚል ጥያቄ ውስጣቹ ከተፈጠረ መልሱ የሚየሆነው በአጭሩ ወጌሻዎች ስለ ሰውነታችን አጥንትና መገጣጠሚያ ; ጡንቻ ; የደም ስር እና ነርቭ
✔️ ጤናማ የሆነ አሰራር ወይም ጤናማ እንቅስቃሴ
✔️ ተፈጥሮአዊ ጤናማ አቀማመጥ
✔️ ከጉዳቱ በኋላ ስላለው የማገገሚያ ተፈጥሮአዊ ሂደቶች
✔️ ስለ ጉዳቱ ትክክለኛ የህክምና አማራጮች እና
✔️ ከህክምናው ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ የግንዮሽ ጉዳቶች ላይ በቂ እውቀት ስሌላቸው ነው።

ይሄን ያልኩበት ምክንያት በጣም ብዙ በተሳሳተ የባህላዊ ህክምና ሲታከሙ የነበሩ በሆስፒታል ውስጥ ከሚታዩት በአሳዛኝ ሁኔታ የእጅ እና የእግራቸውን ጤናማ እንቅስቃሴ ማግኘት ያልቻሉ ብሎም ክፉኛ ከመጎዳቱ የተነሳ ሂወታቸውን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ተብሎ ለመቆረጥ ህክምና የተዳረጉ አዋቂ እና ህፃናት ታካሚዎች የተነሳ ነው።

ይህም የሆነበት ምክንያት ከአደጋው በኋላ ችግራቸው ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ወጌሻ ጋር ሄደው ያመማቸውን አካባቢ ሲታሹ እና በባህላዊ መንገድ ሲታሰሩ ከቆዩ በኋላ ህመሙ ሲብስና ለውጥ ሳይኖረው ሲቀር ብሎም ችግሩ ከተባባሰ እና ለህክምና አስቸጋሪ ከሆነ በኋላ ወደ ጤና ተቋም ይመጣሉ።

በዚህ ጉዳይ ማህበረሰባችንም ላይ መፍረድ አይቻልም ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ይህ ሁኔታ የሚከሰተው ካለማወቅ የተነሳ ነው።

ታዲያ ወደጤና ተቋም መሄድ የሚያስፈልግበትን ምክንያት ለምን እንደሆነ በቀላሉ ላስረዳቹ

  • ለምሳሌ እጃችንን በምናይበት ጊዜ በተፈጥሮ ከላይ ትከሻችን ጀምሮ እስከታች ጣቶቻችን ጫፍ ድረስ በተለያዩ አጥንቶችና መገጣጠሚያዎች ጡንቻዎች የደም ስሮች እና ነርቮች የተገነባ የሰውነታችን አካል ነው። ታዲይ ይሄ እጃችን ጤናማ በሆነ መንገድ ለመስራት የነዚህ መሰረታዊ ክፍሎች ጤናማ መሆን ወሳኝነት አለው ማለትም ከነዚህ አንዱ ክፍል ላይ ጉዳት ከደረሰ እጃችን ለመንቀሳቀስ እና የእለት ተእለት ስራችንን ለመስራት ይቸገራል ማለት ነው።

በእጅ ላይ ጉዳት ከደረሰ የሚታዩት ምልክቶች የተጎዳው አካባቢ ማበጥ መኖር; ከቀላል እስከ ከባድ ህመም መኖር; የቆዳ እና ጡንቻ መበለዝ ወይም መቁሰል መኖር; የእጅ መዞር ወይም መጣመም; የእጅ ማጠፍ መዘርጋት አለመቻል እና የእጅ ለመንቀሳቀስ መስነፍ ሊሆን ይችላል።

እነዚህ የጠቀስኳቸውን ምልክቶች ያለበት ሰው በተገቢው ጤና ባለሞያው ካልተመረመረ በስተቀር በትክክል የትኛው የእጅ ክፍል ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ማወቅ አይቻልም ማለትም እንደ አደጋው ቅለትና ክብደት በአጋጣሚ አንዱ ክፍል ወይም ሁለቱም እንዳንዴም ሁሉም ክፍል ላይ ጉዳት ሊያጋጥም ይችላል።

የትኛው ክፍል እንደተጎዳ ማወቅ ያስፈለገበት ምክንያት የእያንዳነዱ ክፍል ጉዳት ህክምናቸው የተለያየ ስለሆ ነው ማለትም የእያንዳንዱ ክፍል ከአፋጣኝ የቀዶ ህክምና እስከ በቀጠሮ የሚታከም ህክምና ሊያስፈልገው ስለሚችል ነው። ነገርግን አንዱ ክፍል ብቻ አክሞ ሌላውን መተው ዘላቂ የሆነ መፍትሄ አይኖረውም።

በጤና ተቋም ሲሄዱ በዋነኝነት የተጎዳው የሰውነት ላይ አካላዊ ምርመራ እና እንደአስፈላጊነቱ የራጅ ምርመራ ይደረጋል።

ማስተዋል ያለባቹ በአደጋ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ የአጥንት ስብራት አይነቶች ሲኖሩ እንደዛውም የስብራት አይነቶች ህክምናቸው የተለያየ ነው።

የአጥንት ስብራት ካለ ከህክምናውም በኋላ ህክምናው የተሳካ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ድጋሚ የራጅ ምርመራ በማድረግ ይታያል::

ሌላው ነገር አንዳንድ የአጥንት ስብራት አይነቶች እና ስብራቱ አካባቢ የቆዳ መከፈት ወይም የአጥንቱ ወቶ መታየት ካለ አፋጣኝ የሆነ ህክምና ስለሚያስፈልጋቸው በተቻለ መጠን በጊዜ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ተጠቃሚ ያደርጋል።

ስለዚህ በአጠቃላይ አያድርገው እና እርሶ ወይም ልጆ ላይ በተለያየ አጋጣሚ አደጋ አጋጥሞት ጉዳት ቢደርስ ከባህላዊ ህክምና ይልቅ በጊዜ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ከጉዳቱ ጋር በተያያዘ የአጥንት የመገጣጠሚያ የደምስር የነርቭ እና የጡንቻ ላይ ጉዳት መኖር አለመኖሩን መመርመር እና ተገቢውን ህክምና በማግኘት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማግኘት ትችላላችሁ።

👨‍⚕️ ዶ/ር ዮናታን ከተማ: በቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህፃናት ቀዶ ህክምና ሬዚደንት ሐኪም
” ቅድሚያ ለጤናዎ ይስጡ “
🌼 መልካም አዲስ አመት

🔊 ለበለጠ ማብራሪያ እና ምክር 👇👇👇 ይጎብኙ።
Youtube https://youtube.com/@kedmialetenawo?si=i732Q1VUP2p5z2y-

@hakim

Similar Posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *