ዋኪንግ ኮርፕስ ሲንድረም ወይንም በሌላ ስሙ ኮታርድስ ሲንድረም (cotard’s syndrome) በጣም ያልተለመደ የነርቭ እና የአዕምሮ (neuropsychiatric) ችግር ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በ1882 እ.ኤ.አ በፈረንሳዩ የሥነ-አዕምሮ ሐኪም በዶ/ር ጁሌስ ኮታርድ ሲሆን በዋነኝነት የዚህ የአዕምሮ መዛባት ችግር ተጠቂ የሆኑ ሰዎች የተወሰነ የሰውነት ክፍላቸው እንደጎደለ ወይንም እየሞቱ እንዳለ ባስ ሲልም እንደሞቱ እና ህልውናቸውም እንደሌለ አጥብቀው ያምናሉ።
ይህ ችግር ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ የሌሎች የአዕምሮ ሕመሞች ምልክት ሆኖ ይታያል። እስካሁን ድረስ በአለማችን በዚህ ችግር ተጠቅተው ሪፖርት የተደረጉት ወደ 200 የሚጠጉ ኬዞች ብቻ ናቸው።
የዋኪንግ ኮርፕስ ሲንድረም ምልክቶች ምን ምን ናቸው ?
- እየሞትኩ ነው ፣ ሞትቼአለሁ ወይንም ከዚህ በኃላ የለሁም የሚል ቅዠት
- አደገኛ የሆነ ድባቴ ወይንም ትካዜ
- ለህመም ምንም ግብረ-መልስ አለመስጠት
- ከተለያዩ ማኅበራዊ ተግባራት ራስን ማግለል
- አለማውራት እና ዝምታ ማብዛት
- ምግብም ሆነ መጠጥ ከመውሰድ መቆጠብ
- ራስን የመጉዳት ተደጋጋሚ ሙከራዎች
- እየሞቱ እንደሆነ የሚገልፁ ድምፆችን መስማት
- እና ሌሎችም ይገኙበታል ።
የዋኪንግ ኮርፕስ ሲንድረም መንሥዔዎች ምን ምን ናቸው?
የዚህ ችግር ትክክለኛ ምክንያቱ ባይታወቅም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የጤና መቃወሶች አንድ ምልክት ሊሆን ይችላል።
- እስትሮክ
- የደም መርጋት
- የጭንቅላት ጉዳት
- ጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠሩ ዕጢዎች
- ድባቴ (Depression)
- ጭንቀት (Anxiety )
- ሱስ
- ስኪሶፍሬኒያ (schizophrenia )
- ዲመንሺያ
- ኢፕለፕሲ (epilepsy )
- ማይግሬይን
- መልቲፕል ስክሌሮሲስ (multiple sclerosis )
- ፓርኪንሰን
- ጭንቅላት ላይ በሚደርስ አደጋ ምክንያት በሚከሰት የደም መፍሰስ እና የመሳሰሉት።
ዋኪንግ ኮርፕስ ሲንድረም እንዴት ሊታወቅ ይችላል ?
ከላይ እንዳነሳነው ዋኪንግ ኮርፕስ ሲንድረም ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን ሌሎች የአዕምሮ እክሎችን ተከትሎ የሚመጣ የ ህመም ምልክቶች ስብስብ (syndrome) ሲሆን ሀኪሞች ሌሎች ህመሞችን ከመረመሩ እና ሌላ ምክንያት እንደሌለ ሲያምኑ ወደዚህ ድምዳሜ ይደርሳሉ ማለት ነው።
ህክምናውስ ምን ይመስላል ?
በዋናነት ዋኪንግ ኮርፕስ ሲንድረምን ለማከም ችግሩን ያመጣውን መንስዔ ወይም አባባሽ የጤና እክል ማከም ሲሆን ፡ በአባዛኛው የተለያዪ መድኃኒቶችና የስነ-ልቡና ህክምና ዘዴዎች (psychotherapy) ጥቅም ላይ ይውላሉ ።
ለምሳሌ
* ድባቴን ለመቀነስ የሚረዱ መድኃኒቶች (Antidepressants)
* አንቲሳይኮቲክ መድኃኒቶች
* ጭንቀትን ለመቀነስ የሚወሰዱ መድኃኒቶች (anti-anxiety medications )
* ኮግኒቲቭ ቤሄቪሪያል ቴራፒ (CBT)
*በመጨረሻም መድሃኒትና እና ሥነ-ልቡና ዘዴዎች ለውጥ ካላመጡ ጭንቅላት ላይ የሚለቀቁ የኤሌክትሪክ ኮረንቲን በመጠቀም የ አእምሮ ህዋሶችን(brain cell) የማነቃቃት ህክምና (Electroconvulsive therapy) እንደ መጨረሻ አማራጭ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።