የትኛውም አይነት ህክምና በሁለት ወገኖች መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚጠይቅ መሆኑ እሙን ነው። በተለይ የቀዶ ጥገና ህክምና ሲሆን ደግሞ ታካሚው ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ስላሉት የህክምና አማራጮች የያንድአንዱን ጥቅምና ጉዳት የማስረዳት ኃላፊነትና ታካሚው ወደ ውሳኔ እንዲመጣ ማድረግ የሀኪሙ ግዴታ ቢሆንም የመጨረሻ ውሳኔው የታካሚው ይሆናል። በርግጥ አንድ ታካሚ በተለይ የቀዶ ጥገና ህክምና አማራጭ ሲቀመጥለት ከያዘው በሽታ ከመዳኑ ባልተናነስ የሚደረግለት ህክምና በሚኖረው ማህበረሰብ አንፃር እነዴት እንደሚታይና ለፈጥርበት የሚችለውን ማህበራዊ ተፅዕኖ ከበሽታው እኩል ያስጨንቀዋል።
ለዚህም ነው በተለይ አንዳንድ የሚቀርቡላቸውን የህክምና አማራጮችን ወደጎን በመተው ህይወትን እስከማጣት የሚደረሰው። ይህ እንዲፈጠር ትልቁን ሚና የሚጫወተው ደግሞ ስለበሽታውም ይሁን ስለሚሰጠው ህክምና ሕብረተሰቡ ያለው የግንዛቤ ደረጃ ነው። በዚህም የተነሳ በተለይ በሕፃናት ላይ የሚከሰቱ የተለመዱና መታከም የሚችሉ የተለያዩ የሰውነት ክፍል የአፈጣጠር ችግሮች በማህበረሰቡ ግንዛቤ እጥረት የተነሳ ለረጅም ጊዜ ህክምና ሳያገኙ ቤት ተደብቀው ምናያቸው።

በርግጥ የአለም ጤና ድርጅት ጤናን ሲተረጉም የበሽታው መወገድና መዳን ብቻ እንዳልሆነ ያትታል። በተለይ ግለሰቡ ከማህበረሰቡ ጋር ሊፈጥረው የሚችለውን ጤናማ ግንኙነት እንደሚጨምር ያትታል። ይህ ማለት በአጭር ቋነቋ አንድን ግለሰብ ስናክም ስለበሽታውም ሆነ ስለሚደረገው ህክምና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር የህክምናው አካል መሆኑን ነው። ይህም እውን እንዲሆና በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች እንዲሁም የጤና ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ ነው።

ይህን ጽሁፍ እንድፅፍ ያነሳሳኝ በስራ ገበታዬ የገጠመኝ አሳዛኝ ክስተትን መነሻ በማድረግ ትንሽም ብትሆን ግንዛቤ ይፈጥራል ብዬ ያመንኩትን በሆድ ግድግዳ በኩል በሀኪሞች ስለሚበጀው የሰገራ መውጫ (በእንግሊዝኛው Colostomy) ቀለል ባለ ቋንቋ ለማስቀመጥ ሞክራለሁ። ከገጠመኜ ስጀምር እንግዲህ የ5 ወር ዕድሜ ያለው ወንድ ሕፃን ምርመራና ህክምና እንዳደርግለት ራቅ ካለ ሌላ ሆስፒታል ይላካል። በርግጥ ዕድሜው 5 ወር ቢሆነውም ገና እንደተወለደ በ 3ኛ ቀኑ እዛው የተወለደበት ሆስፒታል ውስጥ ቀዶ ጥገና እነደተሰራለት የያዘው መረጃ ይገልፃል።

ቀዶ ጥገናው የተሰራበትም ምክኒያት ሕፃኑ ሲወለድ መፈጠር የነበረበት ሰገራ መውጫ ቀዳዳ (ፊንጢጣ) ባለመፈጠ ምክኒያት በተከሰተው የአንጀት መዘጋት ህይወቱን በጊዜው ለማትረፍ መሰራት የነበረበት በሆዱ በኩል የተደረገ ጊዚያዊ የሰገራ መውጫ ቀዳዳ ነው። በዚህም ቀዶ ጥገና ምክንያት ህይወቱ ተርፋ ለዋናው ቀዶ ህክምና ወደኔ መላኩን ብረዳም በጣም ትኩረቴን የሳበው ግን ሌላ ነበር።
ይህም አንድ ጨቅላ ሕፃን ለፀሐይ ብረሀን (ጨረር) በበቂ ባለመጋለጡ ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶችን ከማየቴም በተጨማሪ በዚሁ ምክኒያት ሰውነቱ እጅግ እንደተጎዳ አስተዋልኩኝ። ይህ የሆነው ደግሞ 13 ወር ሙሉ የፀሐይ ብረሐን በሚታይባት ሀገር መሆኑ ግርም ቢለኝም ምክኒያቱን ለማወቅ ጓጓው።
በመጀመሪያ በርግጥ ወላጅ እናት በበቂ ሁኔታ ለፀሐይ ብረሐን እነደምታጋልጠው ብትነግረኝም የኃላ የኃላ ግን እነደ ዋሸችኝ አመነች።
እውነት ነው ይህ ጨቅላ ሕፃን በማያውቀውና ባልሰራው ሀጥያት ለ5 ወራት በጨለማ ቤት ነበር ያደገው። በዚህም ምክንያት ለፀሐይ ብረሀን በበቂ ሁኔታ እንዳልተጋለጠ ሰውነቱ ይመሰክር ነበር።
ለምን? ብዬ ስጠይቃት ግን ያገኘሁት መልስ ይበልጥ አሳዘነኝ። እንግዲህ ይህ ጨቅላ ህፃን በጨለማ ቤት እንድያድግና ሰውነቱ ከፀሐይ ብረሀን የሚገኘውን ለዕድገቱ ጠቃሚ የሆነውን ጨረር እንዲናፍቅ የሆነው “ሰው ብያየው ምንይለኛል?፣ ምን ብዬስ አስረዳለሁ?” በሚል ሀሳብ መሆኑንና ዘመድ መጥቶ እንኳን ያች ነገር እንዳያዩብኝ ስል አቅፈው እንዳይስሙት ሁሉ ጥረት ስታደርግ እንደነበር አስረዳችኝ።
አዎ እኛ የምንሰጠውን ህክምና ለታካሚው ወይም ለወላጅ በበቂ ሁኔታ ብናስረዳም የማህበረሰቡን የግንዛቤ ደረጃ ካላሳደግን የሰጠነው ህክምና ሌላ ያልተፈለገ መዘዝ ሊያመጣ እንደሚችል ይህ አሳዛኝ ታሪክ ማሳያ ነው። በዚህ አጋጣሚ በ ሆድ በኩል በቀዶ ጥገና ስለሚሰራው የሰገራ መውጫ ቀዳዳ (colostomy) ትንሽ መረጃ ለማካፈል ወደድኩ።
  1.  በሆድ በኩል የሚፈጠር የሰገራ መውጫ ማለት የተወሰነውን የትልቁ አንጀት ክፍል በመለየት ፊትለፊት ከሚገኘው የሆድ ግድግድ ጋር በመስፋትና በሆድ ግድግዳ በኩል በወጣው ትልቁ አንጀት ላይ ቀዳዳ በመፍጠር ሰገራ እንዲወጣ የመድረጊያ ዘዴ ሲሆን አንድ አንዴ በትልቁ አንጀት ምትክ ትንሹ አነጀትም ላይ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ቀዶ ህክምና በሕፃናት ላይ ሲሰራ አብዛኛውን ጊዜ ዋናው ችግር እስኪታከም ብቻ የሚቆይ ሲሆን ከተወሰኑ ወራት በኃላ ግን በቀዶ ህክምና ወደ ቦታው ይመለሳል።
  2. እንዲ አይነት ቀዶ ህክምና በ1710 አካባቢ እንደተጀመረና በየጊዜው ዕውቅናና ተቀባይነት እያገኘ የመጣ መሆኑን የተለያዩ የህክምና ድርሳናት ያስረዳሉ። እንዲሁም በዘመናቸው አለም ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ ታላላቅ ሰዎች በዚህ የቀዶ ጥገና ዘዴ ህይወታቸው እነደተረፈና ይህም ክስተት ሳይበግራቸውና ለስራቸው እንቅፋት ሳይሆንባቸው አለምን በተፅዕኗቸው ስር እንዳቆዩ ይነገራል።

ከነዚህ ዝነኞች መካከልም የፈረንሳይ ታዋቂው ወታደራዊ መሪ የነበረው Napoleon Bonaparte እንዲሁም 34ኛው የ አሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው ባለ 5 ኮከብ ጀነራል Dwight Eisenhower ይጠቀሳሉ። ይህም ቀዶ ጥገናው መሆን ከምንፈልገው ነገር አንዳች እርምጃ ወደኃላ እንደማያስቀረን ማሳያ ነው።

3.  የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እንዲህ አይነት ቀዶ ህክምናዎች በአለም ላይ ከሚሰሩ የቀዶ ጥገና አይነቶች በቁጥር ግምባር ቀደም እንደሆነ ያሳያሉ። በሀገረ አሜሪካ እንኳን በየዐመቱ እስከ 100,000 የሚጠጉ በሆድ በኩል የሚዘጋጁ የሰገራ መውጫዎች እንደሚከወኑ ጥናቶች ይመሰክራሉ። ይህ ማለት በአለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዚህ ቀዶ ጥገና ተጠቃሚዎች እንዳሉ ማሳያ ነው።

4. ይህ ኦፕራሲዮን ከጨቅላ ሕፃናት ጀምሮ አስከ አዛውንት ባለ የዕድሜ ክልል ሊከወን ይችላል። ነገር ግን የሚሰራበት ምክንያት በየዕድሜ ደረጃ ይለያያል።
በሕፃናት ላይ አብዛኛውን ጊዜ ለኦፕራሲዮኑ ምክንያት የሚሆኑት የሰገራ መውጫ አፈጣጠር ችግር ፣ የአንጀት መታጠፍ ወይም በአደጋ ምክንያት የአንጀት መበሳት ወይም የፊንጢጣ ጡንቻ መጎዳት ከብዙ ጥቂቶች ናቸው።
በቀጣይ ክፍል ደግሞ ወላጆች እንዲህ አይነት ቀዶ ጥገና ለተሰራላቸው ሕፃናት ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄና እንክብካቤ ይዤ እመለሳለሁ። አመሰግናለሁ።
ዶ/ር አሻግሬ ገ/ሚካኤል ፤ የህፃናት ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት
ቴሌግራም: t.me/HakimEthio

Similar Posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *