የተዘጋ የአንጎል ደም-ስርን በመክፈት እስትሮክን ለማከም የሚውለው በመርፌ የሚሰጥ መድሐኒት :rTPA

በደም ስር በሚሰጥ መድሐኒት እስትሮክን በማከም ፈር ቀዳጁ የሀገራችን ሆስፒታል ጥቁር አንበሳ ህክምናውን በነፃ እየሰጠ ይገኛል ፤ በብዙ መቶ ሺ የሚሰጥ ህክምና መሆኑን አይዘንጉ ፤

ደም ስር ለአንጎል የኤልክትሪክ ገመድ ለቴሌቢዥን እንደ ማለት ነው ። የደም ስር ምግብና መጠጥ ከልብ ወደ ልዩ ልዩ ክፍለ አካሎች ወስዶ በምላሹ ከነሱ ዳግም ወደ ልብ የሚመላለስበት ማጓጓዣ መስመር ነው ። ክፍትና አስተማማኝ መሆን አለበት ። የኤሌክትሪክ ገመዱ የተቆረጠበት TV መስራት እንደማይችል ሁሉ የደም ስር ያላገኘ አንጎል ክፍልም አይሰራም ። አንጎል የደም ዝውውር መቋረጥን መቋቋም የማይችል የአካል ክፍል ነው ።

እስትሮክን በአመርቂ ሁንታ ማከም ካስቻሉ የህክምና ውጤቶች አንዱ በደም ስር የሚሰጥ ህክምና ነው ። መ’ዳኒቱን በደም ስር ሰጥቶ በአንጎል ውስጥ የተዘጉ ደም ስሮችን መክፈት የሚያስችል የህክምና አይነት ነው ። ከልብ ተነስቶ አለያም በአንጎል ደም ስር ውስጥ በተፈጠረ ደም መርጋት አማካኝነት የተዘጉ ደም ስሮችን መክፈት የሚችለው የጓጎሉና የረጉ ደም ውህዶችን በማሟሟት ነው ። መድሐኒቱ በረመጥ ላይ እንደተጣደ ሞራ እነዚያን የረጉ ደም ውህዶችን ያቀልጣል ፤ በዚህም የደም ስሮቹ ለደም ዝውውር ምቹና አስተማማኝ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ።

መድሐኒቱ ውድ በመሆኑ እና ስለ ገናናነቱ ወይም ፈዋሽነቱ ብዙም ባለመነገሩ (በቅርብ መታወቁ እና የህክምና ጉዟችን በማደግ ላይ በመሆኑም ጭምር ) በሀገራችን በደንብ የሚታወቅ አይደለም ። በሀገራችን ለመጀመሪያ ግዜ በመንግስት ሆስፒታል ይኸንን መድሐኒት ለእስትሮክ ታካሚዎች መስጠት የጀመረው ጥቁር -አንበሳ ሆስፒታል ነው ። ሆስፒታሉ ድንገተኛ የእስትሮክ መታከሚያ ማዕከል በማቋቋም ህክምናውን መስጠት ከጀመረ ሁለት አመታት ተቆጥረዋል ።

የማዕከሉ መከፈት የህክምናውን አመርቂ ውጤት በተግባር ማሳየት በመቻሉ ህክምናውን ማስፋፋት እንደሚገባ አሳይቷል ። እስትሮክ ሰፋ ያለ የማህበረሰብ ችግር ነው ።አስቸኳይ ህክምና መፈለጉ ህክምናው በግዜ የተገደበ መሆኑን ያሳያል ። አንጎል በግዜ የተገደበ ነው ። ያለ ምግብና መጠጥ የአንጎል ህዋሳት በሒወት ሊቆዩ የሚችሉት ለደቂቃዎችና ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ነው ። <ግዜ አንጎል ነው > በሚል መፈክር ነው እስትሮክ የሚታከመው ።

አሁንም እስትሮክ የማይታከም ህመም ፤ የሰይጣን ምት ተደርጎ ይታሰባል ። እስትሮክን ማከምም መከላከልም እንደሚቻል ሳይንስ አረጋግጧል ። ከዚያ በላይ ታክመው የዳኑ የአይን እማኞች በብዙዎቻችን አጠገብ ይገኛሉ ። ያንን ያላደረኩ ከኛ መራቃቸውን እናስታውሳለን ። ችግሩ የግንዛቤ አለፍ ሲልም የአገልግሎት ውስንነት መኖሩ ነው ። ተገቢውን የነቃና የተቀላጠፈ የድንገተኛ ህክምና አሰጣጥ ስረዓት በሁሉም ሆስፒታሎች በመዘርጋት ፤እያንዳንዱን ማህበረሰብ ስለ ህመሙ አስከፊነት እና አስቸኳይነት ግንዛቤ በማስረፅ ተጎጂዎችን በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል እንዲመጡ በማድረግ እስትሮክን በመርፌ በሚሰጥ መድሐኒት ማከም እንደሚቻል እናሳውቅ ።

መድሐኒቱ የሚሰጥበት የግዜ ገደብ አጭር በመሆኑ ተጎጂዎች ቀድመው መድረስ አለባቸው ። እስትሮክ ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚከሰት የእጅና እግር መስነፍ ፣ ፊት መጣመም አለያም የመገዳገድና እረፍት የለሽ ትውከት የሚያስከትል ድንገተኛ አካላዊ የአንጎል ችግር ነው ፤ችግሩ የደም ዝውውር መቋረጥ ነው ።

መድሐኒቱ ውድ በመሆኑ በቀላሉ የሚቀመስ አይደለም ። የጥቁር አንበሳ የነርቭ ህክምና ትት ክፍል ባደረገው ጥረት መድሐኒቱን ከለጋሾች በነፃ ለታካሚዎች እያደረሰ ይገኛል ። ምንም እንኳ ከለጋሽ የሚገኝ ልገሳ ቋሚ ይሆናል ባይባልም ለግዜው ግን ብዙዎችን መታደግ አስችሏል ።ቀጣይ ዘላቂ መፍትሔ በሆስፒታሎች በኩል ከሚመለከተው አካል ጋር ተመካክሮ እንዲቀርብ ግንዛቤውን ለመንግስትም ማስረዳት የባለሙያ ሐላፊነት ነው ።

እስከዚያው ሁሉም ሰው እስትሮክ ታማሚን በአፋጥኝ ህክምና ወዳለበት መሔድ እንደሚገባው ይኸን መልእክት ያሰራጭ፤ ያሳውቅ!

References
Jankovic J, Mazziotta JC, Pomeroy SL, Newman NJ, Bradley WG (Walter G. Bradley and Daroff’s neurology in clinical practice, eight’s edition P 1393-94.

ዶር መስፍን በኃይሉ ፤ ጥቁር አንበሳ

@HakimEthio

Similar Posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *