


የመኪና አደጋ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 29 አመት ለሆኑ ህጻናት እና ጎልማሶች የሞት ዋነኛ መንስኤ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የዕድሜ ክልሎች ውስጥ ስምንተኛው የሞት መንስኤ ነው።
የመኪና አደጋ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ጤና ችግር፣ ለአካል ጉዳትና እና ሞት ከፍተኛ ጫና አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። የተሽከርካሪ ባለቤትነት በፍጥነት መጨመር፣ በቂ ያልሆነ የመንገድ መሠረተ ልማት እና የትራፊክ ህግና ደንቦችን በአግባቡ አለማክበር ሁኔታውን አባብሶታል።
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ ከሆነ ከ2000 ዓ.ም አደጋው በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በአፍሪካ ከፍተኛ የመንገድ ትራፊክ ሞት ካለባቸው ሀገራት አንዷ መሆኑን ያመላክታል።
በ2009 ዓ.ም ብቻ በየ 100,000 ሰዎች 26.7 ሰዎች ላይ የመኪና አደጋ የሚደርስባቸው ሲሆን 4.7 ሰዎች ህይወት ይጠፋል። ከሞት ምጣንም 78 በመቶ ወንዶች ስሆኑ 22 በመቶ ሴቶች ናቸው።
ለአደጋ የተጋለጡ የመንገድ ተጠቃሚዎች መካከል በዋናነት እግረኞች ባልተመጣጣነ ሁኔታ እየጎዳ ይገኛል፣ ይህም ፈጣን ምላሽ አስፈላጊነትን ያሳያል።
የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጽእኖ የህይወት እና የአካል ጉዳት አልፎም; በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና ይፈጥራል። ከህክምና፣ ከመልሶ ማገገም እና ከምርታማነት መጉደል ጋር የተያያዙ ወጪዎች የህዝብ ጤና፣ ሀብቶችን እና የሀገራዊ ኢኮኖሚን ሊጎዱ ይችላሉ።
በአደጋ የተጎዱ ቤተሰቦች በህክምና ወጪዎች እና በገቢ ማጣት ምክንያት የገንዘብ ችግር ያጋጥማቸዋል, ይህም የድህነትን ዑደት ሊያባብስ ይችላል። በተጨማሪም፣ በሕይወት የተረፉ ሰዎች እና ቤተሰቦች ላይ የሚደርሰው የስነ ልቦና ጉዳት የረዥም ጊዜ የአእምሮ ጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።
በኢትዮጵያ የመኪና አደጋን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ምላሽን ይጠይቃል። የመንገድ መሠረተ ልማትን ማሻሻል ፣ የትራፊክ ህጎችንና ተያያዥ ፖሊሲ ማሻሻል እና በጥብቅ መተግበር፣ የትራፊክ ህጎች አክብሮ የማሽከርከር ልምዶች ላይ ያተኮሩ የህዝብ ግንዛቤ ዘመቻዎች ማከናወን፣ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ እንዲሁም በድንገተኛ ህክምና ተደራሽነት ላይ ኢንቨስት ማድረግ። ሀገራችን እነዚህን እርምጃዎች በመውሰድ የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን ሸክም በእጅጉ በመቀነስ ትችላለች።
ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋነው: በድንገተኛና ፅኑ ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር