ስለ ኮሌስትሮል ህመም ስናስብ ብዙውን ጊዜ ከአዋቂዎች ጋር ብቻ እናያይዘዋለን። ነገርግን ይህ የጤና ጉዳይ ህጻናትን እና ታዳጊዎችን ሊያጠቃ ይችላል። በዋናነት ልጆች ላይ የሚከሰት የኮሌስትሮል ህመም አይነቶች በዘር የሚተላለፉ ሲሆኑ በተጨማሪም ከአመጋገብ መዛባትና እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማነስ ጋር በተያያዘም የልጆች ኮሌስትሮል ሊዛባ ይችላል።
በልጆችና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች የኮሌስትሮል ህመም በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ነው። በተለይም ከውፍረት መብዛትና እና ጤናማ ያሆነ የአመጋገብ ልማድ እየተስፋፋ በመምጣቱ ብዙ ልጆች ገና በለጋ እድሜያቸው የኮሌስትሮል ችግር እያጋጠማቸው ነው። የአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና አካዳሚ እንዳለው ከሆነ ከአምስት ልጆች አንዱ ያልተለመደ የኮሌስትሮል መጠን ስላላቸው በኋለኛው ሕይወታቸው ለልብ ሕመም የመጋለጥ እድላቸው ይጨምራል። በልጅነት ጊዜ የኮሌስትሮል መዛባት በተለምዶ ከብዙ አስርት አመታት በኋላ የሚጀምረው አተሮስክለሮሲስ የተባለው የደም ቧንቧዎች መጥበብ ችግር ቀደም ብሎ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። በዚህም ምክንያት በአዋቂዎች ላይ የሚታየው ድንገተኛ የልብ ድካምና ስትሮክ በእንቦቃቅላ ልጆች ላይ ሲከሰት ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
ይህን መሰል የጤና ችግር በጊዜ ለማከም እና እንደ ወላጅ የልጅዎን ጤንነት ለመጠበቅ መንስኤዎቹን፣ ምልክቶችን እና የመከላከያ እርምጃዎችን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው።
በልጆች ላይ የሚከሰት የኮሌስትሮል መዛባት ችግሮች መንስኤዎች
በልጆች ላይ የሚከሰት የኮሌስትሮል መዛባት ችግሮች መንስኤዎችን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። እነዚህም በዘር በሚወረስ የዘረመል ችግር የሚመጣ (Inherited Cholesterol Disorders) እና በሌሎች የጤና ችግሮች ምክንያት የሚመጣ የኮሌስትሮል ችግር (secondary dyslipidemia) ናቸው።
በሌሎች የጤና ችግሮች ምክንያት የሚመጣ የኮሌስትሮል ችግር (secondary dyslipidemia) ሲባል ከሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች ጋር የተያያዘ ሲሆን ነው። ለአብነትም የሆርሞን በተለይም የእንቅርት ሆርሞን ማነስ፣ የኩላሊት ህመም፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ ስኳር ህመም፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብና እንቅስቃሴ አለማድረግ ወይም ጎጂ ሶሶች ሊሆኑ ይችላሉ።
በዘር በሚወረስ የዘረመል ችግር የሚመጣ የኮሌስትሮል መዛባት (familial hypercholesterolemia) በልጆች ላይ በጣም የተለመደው ከፍተኛ የኮሌስትሮል መንስኤ ነው። በዘር የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን ይህም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ በአደገኛ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ መጥፎ ኮሌስትሮል መብዛት ያመጣል። በጄኔቲክ ችግር ምክንያት የህመሙ ተጠቂ ልጆች ጎጂ ኮሌስትሮልን በጉበት በኩል ማጽዳትና ማስወገድ ስለማይችሉ ኮሌስትሮል በደም ቧንቧዎች ውስጥ ይከማቻል። ስርጭቱ በአለም ዙሪያ ከ300 ሰዎች ውስጥ 1 ያህሉን ያጠቃል።
ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ሊያስተውሏቸው የሚገቡ የፋሚሊያል ሃይፐር ኮሌስትሮሌሚያ (familial hypercholesterolemia) ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የፋሚሊያል ሃይፐር ኮሌስትሮሌሚያ (familial hypercholesterolemia) ያለባቸው ልጆች ግልጽ ምልክቶች ላያሳዩ ይችላሉ። ነገር ግን ወላጆች ሊለዩዋቸው የሚችሉ ጥቂት ምልክቶች አሉ።
የመጀመሪያው ተመሳሳይ የቤተሰብ ታሪክ ነው። ከቤተሰብዎ ውስጥ አንድ ሰው የልብ ድካም ወይም ስትሮክ በተለይም ከ55 አመት በፊት ካጋጠመው ልጅዎ በዘር የሚተላለፍ የኮሌስትሮል ችግር ሊጋለጥ ይችላል።
በቆዳና ጅማቶች ላይ ቢጫማ እብጠቶች (xanthoma) የኮሌስትሮል መብዛት ምልክቶች ናቸው። አነዚህ ቢጫማ ስብ የቋጠሩ እብጠቶች ብዙ ጊዜ በአይን፣ በክርን፣ በጉልበት፣ በቁርጭምጭሚት አጠገብ ቋንጃ ላይ ይወጣሉ። የሚከሰቱትም ኮሌስትሮል ከደም ሞልቶ ተርፎ በቆዳና ጅማት ሲከማች ነው።
የልጆች የኮሌስትሮል መጠን ከፍ ካለ በተለይም የጎጂ ኮሌስትሮል መጠን ከ190 ሚ.ግ. በዲሲ ሊትር በላይ ከሆነ ሌላኛው የፋሚሊያል ሃይፐር ኮሌስትሮሌሚያ ምልክት ሊሆን ይችላል።
ይህን ህመም ቀደም ብሎ ማወቅና ማከም በጣም አስፈላጊ ነው። በጊዜ ካልታከመ ልጆች ገና በጨቅላ እድሜያቸው በልብ በሽታ የመጠቃትና የመሞት ዕድላቸው እጅግ ከፍተኛ ይሆናል። በጊዜ ካልታከመ ከ30 ዎቹ ወይም ከ 40 ዎቹ ዕድሜ ማለፍ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ሳይብስ ህመሙ ከታወቀ እና በተገቢው ህክምና ከታከመ የልብ በሽታ የመያዝ እድልን በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅ ማድረግ ይችላል።
የፋሚሊያል ሃይፐር ኮሌስትሮሌሚያ (familial hypercholesterolemia) ለመለየት የኮሌስትሮል ምርመራ መቼ ማድረግ ይመከራል?
ተጋላጭ ለሆኑ ህጻናት በተለይም የቤተሰብ ታሪክ ያላቸው የኮሌስትሮል ምርመራ ገና ከ2 አመት ጀምሮ ማሰራት ይመከራል። ለሌሎች ልጆች በአጠቃላይ ምርመራው በ10 አመታቸው እና እንደገና በ18 አመታቸው ድጋሜ ምርመራ ቢሰራ ይመከራል።
ተጨማሪ ተግባራዊ ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ድህረ ገጽ www.melakutaye.com እና ማህበራዊ ሚዲያዎች @hakimmelaku ይከታተሉ!
telegram https://t.me/hakimmelaku
tiktok https://vm.tiktok.com/ZMhH4rfum/
write me feedback at https://maps.app.goo.gl/twmS9fq7LiG1eRnq9
Telegram/WhatsApp +251921720381
Dr. Melaku Taye (Endocrinologist, Lipidologist at Tikur Anbessa Specialized Hospital, Addis Ababa University)
Get social with Hakim on Youtube: http://www.youtube.com/@Hakim207