በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሙሉ ዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ (Total Hip Replacement ) ተጀመረ!
ለሁለት ታካሚዎቸ የተሳካ የሙሉ ዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ ማድረግ ተችሏል።
በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሙሉ ዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ (Total Hip Replacement) በንዑስ ስፔሻሊስት (Sub specialist) የተጀመረ ሲሆን የአጥንት ህክምና ስፔሻሊስት እና የቀዶ ህክምና ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዶ ዳመስ በግራ ዳሌ የመበስበስ (osteonecrosis) ችግር ተጠቂ ለሆነ የ45 ዓመት እድሜ ያለው ታካሚ ሶስት ሰዓት የፈጀ ስኬታማ ውስብስብ ቀዶ ህክምና ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ከ6 ወር በፊት በግራ ዳሌ አንገት ስብራት ተጠቂ የሆነች የ50 ዓመት እድሜ ያላት ታካሚም እንዲሁ ሁለት ሰዓት የፈጀ ስኬታማ ቀዶ ህክምና እንደተደረገላት ዶ/ር አብዶ አክለዋል።
ታካሚዎቹ ከህክምና በኋላም በመልካም የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ዳይሬክተሩ በቀዶ ህክምናው ለተሳተፉ የህክምና ባለሙያዎች በሙሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

በሆስፒታሉ የአጥንት ህክምና ክፍል ላለፉት ዘጠኝ አመታት ከቀላል የአጥንት ህክምና ጀምሮ፣ ከአደጋ ጋር የተያያዙ የአጥንት ስብራቶች፣ ውልቃቶች እንዲሁም ከፍተኛ እና ውስብስብ ልዩ ልዩ የአጥንት ቀዶ ህክምናዎች እየተሰጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህም ለተመሳሳይ ህክምና የሚደረግ ሪፈራልን በማስቀረት ህብረተሰቡን ከአላስፈላጊ ወጪና እንግልት ከመታደግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚገልጹት ዶ/ር አብዶ የህክምና ክፍሉ እንደ ሲ-አርም እና አርትሮስኮፕ (C-ARM, Arthroscope) ያሉ አዳዲስ የህክምና መሳሪያዎችንና ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ ማሽኖችን በማስገባት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ማህበረሰቡም ይህንን አውቆ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።

Youtube: http://www.youtube.com/@Hakim207?sub_confirmation=1
@HakimEthio