ፕሮፌሰር እያሱ መኮንን እሸቱ
ፕ/ር እያሱ በፋርማሲ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወርቅ ሜዳልያ እ.አ.አ በ1980 ከተመረቁ በኋላ በዚሁ ዩኒቨርስቲ የህክምና ፋኩልቲ ፋርማኮሎጂ ትምህርት ክፍልን በዚሁ ዓ.ም በመቀላቀል የአካዳሚክ ጉዟቸውን የጀመሩ ሲሆን እ.አ.አ በ1985 በቀድሞው ዩጎዝላቪያ በአሁኑ ስሎቬንያ በሚገኘው ሉብልያና ዩኒቨርስቲ በፋርማኮሎጂ የማስተሬት ዲግሪ ከሽልማት ጋር አግኝተዋል።
እ.አ.አ በ1987 በዚሁ ዩኒቨርስቲ የፒ.አች.ዲ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ተመልሰው ሲሠሩበት በነበረው ሕክምና ፋኩልቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ሥራቸውን ቀጠሉ። እ.አ.አ በ1996 የተባባሪ ፕሮፌሰርነትን ማዕረግ ያገኙ ሲሆን እ.አ.አ በ2003 የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ካበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች መካከል ለመጥቀስ ያህል፦
- ለረጅም ዓመታት የፋርማኮሎጂ የት/ክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በኃላፊነት ቆይታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ስዊድን ከሚገኘው ካሮሊንሰካ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን በፋርማኮሎጂ ማስትሬት ዲግሪ ያስጀመሩ ሲሆን በዚህም ፕሮግራም ከ112 ተማሪዎች በላይ በማማከር አስመርቀዋል። በተጨማሪም የፒ/አች.ዲ ፕሮግራም በማስጀመር በዘርፉ ብዙ ከፍተኛ ምሁራን ለማፍራት በተደረገው ጥረት አሻራቸውን አሳርፈዋል፤
- የባዮሜዲካል ምርምርና ስልጠና ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን ለ3 ዓመታት ሠርተዋል። በሃገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዩኒቨርስቲዎች የተመዘገቡ ከሰላሣ የፒ.አች.ዲ. ተማሪዎች በላይ አማክረዋል፤
- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፌሎው በመሆን በአካዳሚው የጤና ቡድን ኮሚቴ በአባልነት አገልግለዋል፤
- በዓለም ባንክ በሚደገፈው የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለሆነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሚገኘው ሲ.ዲ.ቲ አፍሪካ በምክትል ሃለፊነት አገልግለዋል፡፡
- ለተለያዩ የውጭና የሃገር ውስጥ የምርምር መጽሄቶች በኤድቶሪያል ቦርድ አባልነት አገልግለዋል።
- በምርምር ሥነምግባርና በመልካም የህክምና ሙከራ ምግባር (GCP) ለብዙ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት የጤና ምርምር ሥነ ምግባርን ተከትሎ እንዲሠራ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
- በብሔራዊ መድሃኒት አማካሪ ኮሚቴ አባልነት ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል፤ የብሔራዊ የጤና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ካውንስልና የብሔራዊ ምርምር ስነምግባር ግምገማ ኮሚቴ ሰብሳቢና ፀሓፊ በመሆን ከአስር ዓመታት በላይ አገልግለዋል፤ አሁንም የብሔራዊ ምርምር ስነምግባር ግምገማ ኮሚቴ በአባልነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
- ለበርካታ የህክምና ሙከራ ምርምር የምርምር ተሳታፊዎችን ደህንነትና የዳታ ክትትል ኮሚቴ (DSMB) ሰብሳቢና አባል በመሆን ሠርተዋል። ለበርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የምክር አገልግሎት በመስጠት ሙያዊ እገዛ አድርገዋል፡፡ ከነኚህ ድርጅቶች መካከል የፌደራል ጤና ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፤ የባህል ሚኒስቴርና የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ይገኙበታል፤
- በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ፋኩልቲም በተደጋጋሚ ምርጥ የፋርማኮሎጂ መምህርነት ሽልማቶችን አግኝተዋል፤
- ከ24 የሚልቁ የምርምር ፕሮጀክቶችን በመምራት እና የምርምር ፈንድ በመሳብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የምርምር ሥራዎችን በመስራት ከ242 በላይ የሆኑ የምርምር ፅሁፎችን በታዋቂ የምርምር መጽሄቶች አሳትመዋል። የምርምር ፈንድ ካገኙባቸው ተቋማት መካከልም የአውሮፓና አፍሪካ የሕክምና ሙከራ ትብብር (EDCTP)፣ የስዊድን ዓለም አቀፋዊ ልማት ትብብር (SIDA)፣ የኖርዌይ ዓለም አቀፋዊ ልማት ትብብር (NORHED)፤ መድሃኒት ትኩረት ለተነፈጋቸው በሽታዎች ተነሳሽነት ድርጅትና (DNDi)፣ እንዲሁም የዓለም ባንክ ይገኙበታል። ለዚህም ከተሰጧቸው እውቅናዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
o የሞሪንጋና ሌሎች ቅጠሎችን በሻይ መልክ ለስኳር ህመምና ለደም ግፊት ሕክምና እንዲውሉ እንዲያስችል ከተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ የአዕምሮ ንብረት ቢሮ የዩትሊቲ ሞዴል ሰርtፊኬትን አግኝተዋል፡፡
o የምስራቅ አፍሪካ የሌሽማንያሲስ ምርምር መድረክ (LEAP) መስራች ኣባል በመሆን በዘርፉ ለ20 ዓመታት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ከመድሃኒት ትኩረት ለተነፈጋቸው በሽታዎች ተነሳሽነት ድርጅት (DNDi) ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
o ከኢትዮጵያ የፋርማሲ ማህበር የከፍተኛ ተመራማሪ የወርቅ ሜዳልያ ተበርክቶላቸዋል።፤
o ከፍተኛ ውድድር የነበረበትን የዓለም ባንክ ፕሮጀክት ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ስላሸነፉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ እውቅና ሰጥቷቸዋል፤
o አሜሪካን አገር በሚገኘው ፒፕል-ቱ-ፒፕል ተብሎ በሚጠራው ድርጅት በትምህርት፤ ምርምርና ፐብሊክ አገልግሎት ላበረከቱት ሥራ እውቅናን ሰጥቷቸዋል፡፡
o ለረጅም የምርምርና የማስተማር አስተዋፅኦቸው የአቢሲነያ ሽልማት ድርጅት የከፍተኛ ክብር ሎሬት ወርቅ ሜዳልያ አበርክቶላቸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፕ/ር እያሱ መኮንን እሸቱ ለሃገራችን እና ለዩኒቨርሲቲያችን ለሰጡት የረጅም ጊዜ አገልግሎት ይህን የህይወት ዘመን አገልግሎት እውቅና ሽልማት ሲሰጣቸው ከታላቅ ምስጋና እና ክብር ጋር ነው።